FSMMIPA

ዜና

ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማነት የሰለጠነ የሰው ሃይል አስፈላጊ መሆኑ ተጠቆመ

አምራች ኢንዱስትሪውን በሰለጠነ የሰው ሃይል ለመደገፍ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ) ጋር በመተባበር በልብስ ስፌት፣ በቆዳ ጫማና ቦርሳ ስራ ለሁለተኛ ዙር የቴክኒክና የክህሎት ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

ስልጠናው ኢንዱስትሪው ላይ የሚታየውን የበቃ የሰው ኃይል ችግር ለመሙላትና በዘርፉ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚያግዝ የተጠቆመ ሲሆን ስልጠናውም በአዲስ አበባ፣ በቢሾፍቱና በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኙ 4 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እየተሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ሐምሌ 21/2013ዓ.ም በደብረ ብርሃን የሚሰጠውን የልብስ ስፌት ስልጠና የጎበኙት የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬህይወት ወ/ማርያም የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት መጠናከር ለመዋቅራዊ ሽግግሩ መፋጠን ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው፣ በዘርፉ ላይ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ክፍተት በመሙላት የዘርፉን ውጤታማነት ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በዚህ ስልጠናም ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ) በተገኘ የፋይናንስ ድጋፍ የሙያ ክፍተትን መሙላት የሚያስችል የቴክኒክና የክህሎት ስልጠና ለሰልጣኞች መመቻቸቱን ተናግረዋል፡፡ 

የዚህ ስልጠና ዋነኛ ዓላማም ወጣቶችን በማሰልጠን ለአምራች ኢንዱስትሪው የበቃና የሰለጠነ የሰው ሃይል በማቅረብና የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታሳቢ ያደረገ ነው ያሉት ወ/ሮ ፍሬህይወት ሰልጣኞች ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ ከኢንዱስትሪዎች ጋር እንዲተሳሰሩ እየሰራለን እንገናለን ብለዋል፡፡ 

በሰልጣኞች የተመረቱ አልባሳትን በቦታው ተገኝተው የተመለከቱት ም/ዋ ዳይሬክተሯ ከተዘጋጁ አልባሳት በመነሳት ሰልጣኞች ጥሩ የስልጠና ቆይታ እንደነበራቸውም መመልከት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን የሚጠይቅ በመሆኑ ባለስልጣኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል ይህንንም አጠናክሮ የሚቀጥልበት እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ 

በደብረ ብርሃን ከተማ በልብስ ስፌት እየሰለጠኑ የሚገኙ ሰልጣኞች በበኩላቸው በተመቻቸለት የስልጠና ዕድል ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፤ ከንድፈ ሀሳብ ጀምሮ በፓፐንት ፣በዲዛይን፣ በቅድና ሙሉ ልብስ ሰፍቶ እስከማጠናቀቅ ድረስ ያለውን እውቀት ማግኘታቸውንና የተለያዩ አልባሳትን ለማዘጋጀት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም ይላሉ ሰልጣኞች መንግስት ከስልጠናው ጎን ለጎን ስራ የሚፈጥሩነትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡ 

በዚህ ዙር 107 ለሚሆኑ ወጣቶች በልብስ ስፌት፣ በቆዳ ጫማና ቦርሳ ውጤቶች እየሰለጠኑ ሲሆን ሰልጣኞች ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ የሙያ ሰርትፍኬት የሚያገኙ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይም በአንደኛው ዙር 93 ሰልጣኞች ስልጠናቸውን አጠናቀው መመረቃቸው ይታወቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *